ኢትዮጵያን ከጂቡቲ የሚያገናኘው የ3.9 ቢሊዮን ብር መንገድ ግንባታ ለቻይና ኩባንያ ተሰጠ

Published: Monday, 15 September 2014 Written by Reporter Sunday 14 September , 2014

ኢትዮጵያን ከጂቡቲ የሚያገናኘው 3.9  ቢሊዮን ብር መንገድ ግንባታ ለቻይና ኩባንያ ተሰጠ 

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን 220 ኪሎ ሜትር መንገድ በ3.9 ቢሊዮን ብር እንዲገነባ፣ ለቻይናው ኩባንያ ሲጂሲ ኦቨርሲስ ፕሮጀክቱን ተፈራርሞ አስረክቧል፡፡ 

ለዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ለሲጂሲ ኦቨርሲስ ከሚከፈለው ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ከቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት (ኤግዚም) ባንክ በብድር፣ 15 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፈናል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲሆን፣ ከአዋሽ-ሚሌ-ጂቡቲ ቀጥሎ ሁለተኛው የገቢና ወጪ ኮሪደር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአዋሽ-ሚሌ-ጂቡቲ ኮሪደር ላይ ይደርስ የነበረው የትራፊክ መጨናነቅና የጉዞ ርቀት ችግር በአዲሱ መንገድ ግንባታ ይፈታል፡፡

የድሬዳዋ-ደወሌ-ጂቡቲ መንገድ በዋናኝነት የምሥራቁን የአገሪቱ ክፍል ከጂቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኝ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክፍልና እንዲሁም ማዕከላዊ ኢትዮጵያን ከምሥራቃዊው የአገሪቱ ክፍሎች ጋር ያገናኛል ተብሏል፡፡ 

የዚህ መንገድ አካል የሆነው የሚኤሶ-ድሬዳዋ መንገድ ግንባታ እንደሚካሄድ ሲጠበቅ፣ የሚኤሶ-ጂቡቲ መንገድ ለኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ መቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና መንገዱንም እንደሚያሳጥር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 

መንግሥት የድሬዳዋ ከተማን የኢንዱስትሪ ፓርክ የማድረግ ዕቅድ እንዳለው ይገልጻል፡፡ በከተማው በተከለለው የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ፣ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ኢንቨስት በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ድሬዳዋና በዙሪያዋ የሚገኙ አካባቢዎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ስለሚታወቁ፣ ከዚህ ቀደም ይህንን ምርት ወደ ጂቡቲ ለመላክ ቢሞከርም፣ መንገዱ አስቸጋሪ በመሆኑና ምርቱ ደግሞ በቀላሉ ለብልሽት የሚዳረግ በመሆኑ፣ ወደ ጂቡቲ ለመላክ አስቸጋሪ እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን በአስፓልት ደረጃ መንገዱ እንዲገነባ መወሰኑ በአካባቢው ኢኮኖሚ መነቃቃት ሊፈጥር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የዚህን መንገድ የውል ስምምነት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልና የሲጂሲ ኦቨርቪስ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ማስተር ኪን ሊጂንግ ተፈራርመዋል፡፡ ይህ መንገድ በሦስት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

 

Reporter Sunday 14 September , 2014

Hits: 822