የመንገዶች ባለሥልጣን ቀጣይ ተሿሚ ለመሆን ባለሥልጣናት ፍላጎት እያሳዩ ነው ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ተሰየመ

Published: Thursday, 06 November 2014 Written by Reporter , Wednesday 06 November, 2014 Page 01

 

Note : You need an Amharic Reader to read this content

ከአቶ  ዛይድ  ወልደገብርኤል  መነሳትበኋላ ፣  ቀጣዩ  የኢትዮጵያ  መንገዶች  ባለሥልጣን  ዋና  ዳይሬክተር  ሆኖ  የሚሾመው  ሰው  ጉዳይ  ላይ  ከፍተኛ  የመንግሥት  ባለሥልጣናት  ፍላጐት  እያሳዩ  መሆኑን  ምንጮች  ገለጹ፡፡

________________________

መንገዶች ባለሥልጣንን ከመስከረም 27 ቀን 1996 ዓ.ም. ጀምሮ በዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዛይድ፣ በትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ጥያቄ መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ ጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣ ደብዳቤ መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ 

አቶ ዛይድ በመነሳታቸው ምክንያት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አቶ ዛይድን የሚተካው ሰው ማን ይሁን በሚለው ጉዳይ መደበኛ ባልሆኑ የውይይት መድረኮች እየመከሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ፣ አቶ ዛይድ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ካደረጉ በኋላ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የሰው ኃይልና የፋይናንስ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ሲሳይ በቀለ በተጠባባቂነት የዋና ዳይሬክተሩን ሥራ ደርበው እንዲሠሩ ሾመዋቸዋል፡፡ 

አቶ ሲሳይ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን፣ የኦሕዴድ አባል ናቸው፡፡ አቶ ወርቅነህ፣ አቶ ሲሳይን ከሾሙ በኋላ ለሥራ ጉዳይ ኦስትሪያ ቪየና በመጓዛቸው በተፈጠረው ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተክለ ጻድቅ ዳባ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የማኔጅመንት አባላትን ጽሕፈት ቤታቸው በመጥራት፣ ተረጋግተው ዕለታዊ ሥራቸውን እንዲያካሂዱ ማሳሰቢያ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት እየተመደበለት በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የሚያካሂድ ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡

ይህ ግዙፍ ተቋም ከፍተኛና ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ አውታሮችን የሚዘረጋ እንደመሆኑ፣ ሁሉም የፌዴራል የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የክልል መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለየመጡበት አካባቢ መንገድ እንዲገነባላቸው በየጊዜው ፍላጐታቸውን ሲያስታውቁና ባለሥልጣኑንም ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ 

ምንጮች እንደሚገልጹት እነዚህ መንግሥታዊ ባለሥልጣናት በሚቀጥለው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተሿሚ ላይ የራሳቸውን ተፅዕኖ ለማሳደር እየተንቀሳቀሱ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ 

ነገር ግን የመንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ከኃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ላይ በግልጽ ባይቀመጥም፣ ለቻይና ኮንትራክተሮች በተሰጡ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ምክንያት መነሳታቸውን ምንጮች እየገለጹ ነው፡፡ አንዳንድ የቻይና ኩባንያዎች ቀደም ሲል በተሰጣቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ያሳዩት የሥራ አፈጻጻም ዝቅተኛ ሆኖ እያለ፣ ተጨማሪ ሥራ ተሰጥቷቸዋል በሚል ምክንያት መግባባት ባለመቻላቸው አቶ ዛይድ መነሳታቸውን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ በግልባጭ ደግሞ ለሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጻፉት ደብዳቤ፣ የአቶ ዛይድን መነሳት አስታውቀዋል፡፡

‹‹መሥሪያ ቤታችሁ (ትራንስፖርት ሚኒስቴር) ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በቁጥር ም/79 በጻፈው ደብዳቤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በአዲስ አመራር በመተካት የለውጥ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል በማስፈለጉ፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የቆዩትን አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ ከጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነት እንዲነሱ ጠይቋል፤›› በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ለአቶ ዛይድ መነሳት የትራንስፖርት ሚኒስቴር መነሻ መሆኑን ገልጿል፡፡

ትራንስፖርት ሚኒስቴር ጥያቄ በጠየቀ በማግስቱ ጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄውን ተቀብለዋል፡፡

‹‹በዚህ መሠረት አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል ከመስከረም 27 ቀን 1996 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ እያመሰገንኩ፣ ከጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው የተነሱ መሆኑን አስታውቃለሁ፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማቸውን በማኖር አቶ ዛይድን ማንሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርብ የአቶ ዛይድን ምትክ እንደሚሾሙ ይጠበቃል፡፡ 

This content is published on Reporter , Wednesday 06 November, 2014 Page 01

Hits: 663