የቻይና ኩባንያ የአዲስ አበባ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ተመረጠ

Published: Monday, 17 November 2014 Written by Reporter Sunday 16 November 2014 Page: 01

Amharic Reader needed for this content.

- ኩባንያው በአምስት ዓመት 116 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል

በመገንባት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ሲጠናቀቅ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱንና ጥገናውን የሚያከናውን ሁለት የቻይና ኩባንያዎች በጥምረት የመሠረቱት የጋራ ድርጅት ተመረጠ፡፡
___________________


ድርጅቱ ኮንሰርቲየም ኦፍ ቻይና ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ (CREC) ኤንድ ሸንዘን ሜትሮ ግሩፕ የሚል መጠሪያ ያለው መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጄ ተፈራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሲአርኢሲ የተሰኘው ኩባንያ በአሁኑ ወቅት የቀላል ባቡር መስመሩን አጠቃላይ ፕሮጀክት በ475 ሚሊዮን ዶላር እየገነባ የሚገኝ ነው፡፡
ሸንዘን ሜትሮ ግሩፕ የተሰኘው ሌላኛው የጥምረቱ ኩባንያ ደግሞ ሸንዘን በምትባለው የቻይናዋ ከተማ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ መሆኑን አቶ ደረጄ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለተመረጡ ኩባንያዎች ብቻ ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ሁለቱ ኩባንያዎች በጥምረት የመሠረቱት ድርጅት መመረጡንና ሥራውንም ለአምስት ዓመታት እንደሚያከናውን ለዚህም ኮርፖሬሽኑ 116 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍል አቶ ደረጄ ገልጸዋል፡፡
የኮንትራት ፊርማው በቅርቡ እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ ደረጄ፣ ኩባንያው የሚያሳትፋቸው ሠራተኞች ብዛት 686 እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ውስጥ 290 ቻይናውያንና 396 ኢትዮጵያውያን ማለትም 48 በመቶ ቻይናውያን 52 በመቶ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛው ዓመት የኮንትራት ዘመን የሚሳተፉ ቻይናውያን ወደ 24 በመቶ ዝቅ እንደሚልና የኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ 76 በመቶ እንደሚያድግ፣ በሦስተኛው ዓመት የሥራ ወቅት ደግሞ የቻይናውያን ሠራተኞች ድርሻ ወደ 13 በመቶ ዝቅ ብሎ የኢትዮጵያውያን ድርሻ ወደ 87 በመቶ ከፍ እንደሚል ከአቶ ደረጄ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአራተኛውና አምስተኛው (የመጨረሻው ዓመት) ኢትዮጵያውያን መቶ በመቶ የሚቆጣጠሩት ሲሆን፣ የተቀጠረው ኩባንያ ሚና ከኋላ ሆኖ ቴክኒካል ድጋፍ የማድረግ ብቻ እንደሚሆን አቶ ደረጄ ተናግረዋል፡፡
በኮንትራቱ መሠረት የቻይናው ኩባንያ ሸንዘን ሜትሮ ግሩፕ በሸንዘን ከተማ ተግባራዊ ያደረገውን ቴክኖሎጂ በሙሉ በአዲስ አበባ የባቡር ትራንስፖርት ላይ ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበትም አቶ ደረጄ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2015 ማለትም ከሁለት ወር ተኩል በኋላ የኮንትራት ውሉ ማብቃት ያለበት ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ካለበት ደረጃ በመነሳት በኮንትራቱ ወቅት እንደማይጠናቀቅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች በወቅቱ ፕሮጀክቱ እንደሚጠናቀቅ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቱ በወቅቱ ካልተጠናቀቀ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ተጨማሪ ወጪውን ከቻይናው ሲአርኢሲ ኩባንያ የመጠየቅ መብት በኮንትራቱ መሠረት አለው፡፡

This content is published on, Reporter Sunday 16 November 2014 Page: 01

 

Hits: 745