ለአዲስ አበባ ባቡር የቻይና ኩባንያ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ተስማማ

Published: Wednesday, 19 November 2014 Written by Reporter Wednesday 19 November 2014 Page: 01

Amharic Reader needed for this content.

ግዙፉ የቻይና ኩባንያ ስቴት ግሪድ እህት ኩባንያ የሆነው ቻይና ኤሌክትሪክ ኢኪውፕመንት እና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት አራት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እንዲገነባ ተመረጠ፡፡
___________________

ኩባንያው በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ሥራውን አጠናቆ ለማስረከብ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ባለፈው ዓርብ ስምምነት ማድረጉ ታውቋል፡፡
ኩባንያው ለዚህ ሥራው የሚያስፈልገው ገንዘብ ለጊዜው ባይገለጽም፣ ፋይናንሱ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በብድር እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
አራቱ የማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚገነቡት፣ ከባቡር መስመሮቹ መነሻ በቅርብ ርቀት ላይ ሲሆን፣ ከዚህ የማከፋፈያ ጣቢያ ተስቦ በሚመጣ መስመር ባቡሮቹ እንደሚንቀሳቀሱ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጄ ተፈራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መሥርያ ቤታቸው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ስምምነት አለው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለባቡር ትራንስፖርቱ ኃይል ያቀርባል ብለዋል፡፡
የባቡር ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሥራ ለመጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮጀክቱም የዚሁ የመጨረሻ የፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ሥራ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የስቴት ግሪድ እህት ኩባንያ በቅርቡ ሙሉ ኃይሉን ተጠቅሞ ግንባታውን በተሰጠው ጊዜ ለማጠናቀቅ የብድሩን መለቀቅ እንደማይጠብቅ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው ግዙፍ በመሆኑ የራሱን የፋይናንስ ምንጮች ተጠቅሞ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡
ስቴት ግሪድ የኢትዮጵያውያን ምልክት በሆነው ዓባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይም ተሳታፊ ነው፡፡ ኩባንያው የህዳሴው ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኃይል ማከፋፈያና ማሠራጫ መስመሮችን በ1.2 ቢሊዮን ዶላር በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ግዙፍ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር እንደተፈራረመ ከኤግዚም ባንክ የሚለቀቀውን ብድር ሳይጠብቅ ወደ ሥራ የገባ ኩባንያ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ለባቡር ፕሮጀክቶቹ ኃይል ለማቅረብ በርካታ ኩባንያዎች ፍላጎት ቢያሳዩም የቀረው ጊዜ አጭር በመሆኑ በርካቶች ወደኋላ ማፈግፈጋቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን ይህ ኩባንያ በፕሮጀክቱ ለመሳተፍ ይሁንታውን መግለጹ ለጉዳዩ ቅርበት ላላቸው ባለሙያዎች አስደማሚ ክስተት ሆኗል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ግንባታው ውስብስብና ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ወደኋላ ማፈግፈጋቸው በመገለጹ ነው፡፡ 34.25 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት 41 ማውረጃና መጫኛ ጣቢያዎች ይኖሩታል፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት 475 ሚሊዮን ዶላር ከቻይናው ኤግዚም ባንክ የተገኘ ሲሆን፣ ከኤሌክትሪክ አቅርቦቱ በስተቀር ሁሉም ፕሮጀክቶችን በበላይነት የሚያካሂደው (ኢፒሲ ኮትራት) ቻይና ሬይል ዌይ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነው፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት፣ በጥር ወር ሥራው ይጀምራል የሚል ዕቅድ ተይዟል፡፡

This content is published on, Reporter Wednesday 19 November 2014 Page: 01

 

 

Hits: 728