በሲሚንቶ የሚገነባው የ130 ሚሊዮን ብር መንገድ

Published: Wednesday, 19 November 2014 Written by Reporter Sunday November 16 2014 Page: 12

Amharic Reader needed for this content.

በአገሪቱ የመንገድ ግንባታ ታሪክ አዲስ የተባለውና በሲሚንቶ ኮንክሪት እየተገነባ ያለው አስር ኪሎ ሜትር መንገድ በበጀት ዓመቱ መ ጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
___________________

የሲሚንቶ ኮንክሪት የመንገድ ሥራ ግንባታን በቀዳሚነት ከጀመረው የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ለሙከራ ተብሎ የተጀመረው የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡
በሲሚንቶ ኮንክሪት ግንባታው የተጀመረው መንገድ በጫንጮ-ደርባ-በቾ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሥር ይገኛል፡፡ በ643.9 ሚሊዮን ብር ወጪ ይገነባል የተባለው የጫንጮ-ደርባ በቾ መንገድ ፕሮጀክት 31.1 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አስር ኪሎ ሜትሩ በሲሚንቶ ኮንክሪት ደረጃ የሚሠራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በመንገድ ግንባታ ዘርፍ በአስፓልት፣ በኮንክሪትና በጠጠር ከመገንባት ባሻገር በአማራጭነት በሲሚንቶ ኮንክሪት ግንባታ ማካሄድ እንዲቻል ታስቦ የአሥር ኪሎ ሜትር የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ለማሳያነት እንዲገነባ መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የጫንጮ ደርባ በቾ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰለሞን ደመቀ እንደገለጹት፣ በሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ግንባታው እስካሁን 2.1 ኪሎ ሜትር ተሠርቷል፡፡ ቀሪው ስምንት ኪሎ ሜትር ደግሞ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በ34 ሴንቲ ሜትር ውፍረት እየተሠራ የሚገኘው የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ውጤት ታይቶ ወደፊት ሌሎች ፕሮጀክቶችንም መሥራት የሚቻልበትን ዕድል ሊጠቁም ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ ኢንጂነር ሰለሞን ገለጻ፣ በሲሚንቶ ኮንክሪት የሚሠራው መንገድ በአስፓልት ከሚሠራው መንገድ የበለጠ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ከረዥም ጊዜ ጥቅም አኳያ በሲሚንቶ ኮንክሪት የሚሠሩ መንገዶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጡ ይናገራሉ፡፡
አንድ ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ለመሥራት አንድ ሚሊዮን ብር ቢጠይቅ በሲሚንቶ ኮንክሪት መሥራት ግን 1.6 ሚሊዮን ብር ሊያስወጣ ይችላል፡፡ ይህም የሲሚንቶ መንገድ የዋጋ ብልጫ ቢኖረውም የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ የአገልግሎት ዘመን ረዥም መሆኑና በቀላሉ ለመጠገንና ማስተካከል የሚያስችል መሆኑ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገዶች ተመራጭ እንዲሆኑ ሰፊ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡
ወደፊት የሲሚንቶ ዋጋ እየቀነሰ ይመጣል የሚል እምነት ስላለ፣ በሲሚንቶ ኮንክሪት የሚሠሩ መንገዶች አሁን ከሚጠይቁት ወጪ ባነሰ ሊሠሩ እንደሚችሉ ኢንጂነር ሰለሞን ተስፋ አላቸው፡፡
ከሲሚንቶ የሚሠራው መንገድ የሙከራ ሥራው ታይቶ በዘላቂነት ሊሠራበት ከቻለ፣ ለአስፓልት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በመቀነሱ በኩል አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ በሲሚንቶ ኮንክሪት የሚሠሩ መንገዶች በአስፓልት ኮንክሪት ከሚገነቡ መንገዶች የበለጠ ወጪ የሚጠይቁ ቢሆንም ለአገልግሎት ከዋሉ በኋላ ከአርባ ዓመት በላይ ያለ ጥገና ማገልገል እንደሚችሉ ነው፡፡ በመሆኑም ለመንገድ ጥገና የሚወጣውን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳሉ፡፡
በአንጻሩ አስፓልት ኮንክሪት የሚሠሩ መንገዶች ከሲሚንቶ ባነሰ ዋጋ ቢገነቡም የመንገዱ ዕድሜ ከ10 እስከ 15 ዓመት ያልበለጠ፤ በመካከል ላይም የሚጠይቀው የጥገና ወጪ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ወደፊት እንደ አማራጭ ሆኖ መቅረብ ይችላል ተብሏል፡፡
በአስፓልት ኮንክሪት የሚሠሩ መንገዶች ለጥገና የሚያስፈልጉት ግብዓቶች ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሚጠይቁ ከመሆናቸው አኳያም የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ከዚህ ጥቅሙ በመነሳትም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡ በተለይ በአገሪቱ ውስጥ በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እየተገነቡ ከመሆኑ አኳያ የወደፊት መሸጫ ዋጋው አነስተኛ ይሆናል እየተባለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንገዶች የሚገነቡት በተለያየ ደረጃ በአስፓልትና በጠጠር ሲሆን፣ የሲሚንቶ ኮንክሪት በብዛት የሚታየው በአውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ብቻ እንደነበረ ተጠቅሷል፡፡
ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በጫንጮ-ደርባ በቾ መንገድ ፕሮጀክት ሥር የተካተተው የሲሚንቶ የኮንክሪት ከመገንባቱ በፊት በበሰቃ አካባቢ በተመሳሳይ የአንድ ኪሎ ሜትር መንገድ ኮርፖሬሽኑ መገንባቱን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

This content is published on, Reporter Sunday November 16 2014 Page: 12

 

 

Hits: 714