አስተዳደሩ የሊዝ አዋጁ እንዲሻሻል ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቀረበ

Published: Monday, 24 November 2014 Written by Reporter Sunday 23 November 2014 Page: 01

Amharic Reader needed for this content.

የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ አቅም ያላቸው ኢንቨስተሮችን ማስተናገድ አላስቻለኝም ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አ ዋጁ እንዲሻሻል ሐሳብ አቀረበ፡፡
___________________

አስተዳደሩ በተለይ ባለኮከብ ሆቴሎች፣ ግዙፍ ሪል ስቴቶች፣ ሆስፒታሎችና የትምህርት ተቋማቶችን ግንባታ ለማካሄድ ኢንቨስተሮች የሚያቀርቡለትን ጥያቄ በድርድር አግባብ ማስተናገድ ባለመቻሉ ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማቅረቡ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው፣ አዋጁ እንዲሻሻል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን መጠየቃቸውን አረጋግጠው፣ አስተዳደሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኅዳር 18 ቀን 2004 ዓ.ም. የከተማን ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ፕሮጀክቶች ለማስተናገድ ክፍተት እንዳለው በዚያው ወቅት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማሳሰቢያ እየተሰጠበት እንደነበር ይታወሳል፡፡
በአዋጁ በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ ፕሮጀክቶች በመንግሥት ባለቤትነት የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡
ነገር ግን ባለኮከብ ሆቴሎች፣ ሪል ስቴቶች ሆስፒታሎችና የትምህርት ተቋማት በልዩ ሁኔታ እንደሚስተናገዱ በግልጽ አይደነግግም፡፡
ይልቁኑ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ በተዘጋጀው ደንብና መመርያ እነዚህ ግዙፍና ለከተማው ፋይዳ ያላቸውን ፕሮጀክቶች በልዩ ሁኔታ ማስተናገድ የሚቻልበትን መንገድ ለማካተት ተሞክሯል፡፡
በአዋጅ የሌለ ነገርን በደንብና መመርያው ውስጥ ማካተት በኢትዮጵያ ከተቀመጠው የሕግ ተዋረድ መርህ አንፃር የሚያስኬድ እንዳልሆነ የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ደንብና መመርያ በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ማስፈጸሚያ ዝርዝር ጉዳይ ከማቀፍ ውጪ አዲስ ድንጋጌ መያዝ ሕገወጥ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡ የአስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ተንታኞችም አሳማኝ አሠራር አለመሆኑን ይቀበላሉ፡፡
ይልቁኑ በባለሞያዎችና በከተማው ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አለመግባባት የፈጠረ ሲሆን፣ የተወሰኑ ባለሙያዎች ሥራቸውን እንዲለቁ ምክንያት መሆኑን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ከፍተት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለሙያዎችን መድቦ አስጠንቷል፡፡ አቶ አሰግድ፣ ኅዳር 2006 ዓ.ም ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና በሥሩ ለሚገኙ መሥሪያ ቤቶች በጻፉት ደብዳቤ፣ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት አሰጣጥ ላይ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥናት ማካሄድ በመፈለጉ ትብብር እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
‹‹የጥናቱ መካሄድ የአሠራር ሥርዓታችን ክፍተት ካለው ከወዲሁ መፈተሽ እንዲቻልና የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ ይረዳናል፤›› በማለት መሥሪያ ቤቶቹ ለኮሚሽኑ ሥራ መቃናት ትብብር እንዲያደርጉ አቶ አሰግድ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥናቱን ካካሄደ በኋላ አዋጁ ደንቡና መመርያው ክፍተት እንዳለውና መጣጣም እንዳለበት ለአስተዳደሩ የጥናቱን ውጤት ገልጿል፡፡
ጥናቱ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች መስተንግዶ መመርያ ቁጥር 15/2005፣ የከተማ መሬት ሊዝ ደንብ፣ ከሊዝ አዋጁ ቁጥር 721/2004 ጋር ይቃረናል ከማለቱ በተጨማሪ፣ የመመርያው አንዳንድ አንቀጾች በአፈጻጸም ወቅት አሻሚ ትርጉም እንዳይሰጣቸው፣ ከሊዝ አዋጁ ጋር ተዛማጀ የሆኑ አንቀጾችን በማጣቀስና ለትርጉም የሚዳርጉ የመመርያው አንቀጾች፣ በሊዝ አዋጁ ከተደነገጉ መሠረታዊ ዓላማዎች ጋር ቢጣጣሙ መልካም እንደሆነ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ለከተማው አስተዳደር በርካታ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ቢቀርቡም፣ በሕግጋቱ አለመናበብ ምክንያት አስተዳደሩ ጥያቄዎቹን ማስተናገድ እንዳልቻለ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንዲሻሻል የሚፈለገው ጉዳይ አገራዊ ፋይዳ አላቸው የተባሉ የኢንቨስትመንት ዓይነቶች፣ በግልጽ ተተንትነው በሊዝ አዋጁ እንዲካተቱ ለማድረግ እንደሆነ ታውቋል፡፡

This content is published on, Reporter Sunday 23 November 2014 Page: 01

 

Hits: 768