ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በመተባበር የባቡር አካዳሚ ልትገነባ ነው

Published: Wednesday, 03 December 2014 Written by Reporter Wednesday December 2014 Page: 01

Amharic Reader needed for this content.

የኢትዮጵያ መንግሥት ከቻይና ጋር በመተባበር በአፍሪካ ቀዳሚ የ ሚሆን የባቡር አካዳሚ በአዲስ አበባ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገለጸ፡፡ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ቦርድ
___________________

ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር አርከበ እቁባይ ባለፈው ማክሰኞ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ የተመረጡ ኩባንያዎች ስምምነት ሲፈርሙ በተገኙበት ወቅት ነው የመንግሥትን ዕቅድ ይፋ ያደረጉት፡፡
ከፊርማው ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ሪፖርተር ስለአካዳሚው ያነጋገራቸው ሲሆን፣ አካዳሚውን የመገንባት ሥራ ሙሉ በሙሉ በዚህ ዓመት እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡
በእስካሁኑ ጥረት ማዕከሉን የመገንባትና የመምራት ኃላፊነት የሚኖረውን ኩባንያ ለመምረጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደወጣና ሦስት የቻይና ኩባንያዎች ተመርጠው ግምገማ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አካዳሚው በባቡር ትራንስፖርትና መሠረተ ልማት ግንባታ ከአስተዳደር ጀምሮ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በኦፕሬሽን፣ በጥገናና በመሳሰሉት ሁሉን አቀፍ ሥልጠና የሚሰጥ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ከተመረጡት ኩባንያዎች ብቃት ያለው አንዱን የመለየት ሥራ በሚቀጥለው ወር መጨረሻ ድረስ ይታወቃል ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ የሚመረጠው ኩባንያ ማዕከሉን ከመገንባትና ከማደራጀት በተጨማሪ ማዕከሉን የሚመሩና አሠልጣኝ መምህራንን ይዞ የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ዓመታት አካዳሚውን ያስተዳድራል ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከቻይኖቹ ጋር በመሆን ልምድ ይወስዳሉ፡፡ ከተወሰነ ዓመት በኋላ ምናልባትም ከአምስት ዓመት በኋላ አካዳሚውን ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን ይመሩታል፤›› ብለዋል፡፡
አካዳሚው ሲቋቋም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታይና አቅም የሚፈጥር እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጐት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር አርከበ፣ የዚህ ምክንያትም አካዳሚው የሰው ኃይል የሚያፈራው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አገሮችም ምርጫቸው የሚያደርጉት እንዲሆን ነው ብለዋል፡፡ ይህ መሆን እንደሚችል ደግሞ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን አካዳሚ ስኬት ልምድ መውሰድ ይቻላል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሥር ያለው የሰው ኃይል ዘጠና በመቶ ለባቡር ትራንስፖርትና መሠረተ ልማት ዝርጋታ አዲሶች በመሆናቸው፣ መንግሥት ክፍተቱን ለመሙላት ከ250 በላይ ወጣት ኢንጂነሮችንና ቴክኒሺያኖችን በመመልመል በቻይናና በሩሲያ አገር እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት በዓመቱ መጨረሻ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ፕሮጀክት ትራንስፖርትና ጥገና ሁለት የቻይና ኩባንያዎች የፈጠሩት ጥምረት እንዲመሩት ተደርጓል፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች በቻይናዋ ሸንዘን ከተማ የባቡር ትራንስፖርት የሚሰጠው ሸንዘን ሜትሮ ግሩፕና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ግንባታን የሚያከናውነው ቻይና ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ (CREC) ናቸው፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች በቻይና መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደሩ ሲሆን፣ የሁለቱም ኩባንያዎች የቦርድ ሊቀመንበሮች በተገኙበት እንዲሁም በኢትዮጵያ በኩል ዶ/ር አርከበና ሌሎች የቦርድ አባላት ባሉበት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስምምነቱን ከሁለቱ ኩባንያዎች ጋር ፈርመዋል፡፡
የሁለቱ ኩባንያዎች ጥምረት የባቡር ትራንስፖርትና ጥገናውን ለአምስት ዓመት የሚያከናውኑ ሲሆን፣ በቆይታቸውም 116 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ፡፡
ኩባንያዎቹ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያሳትፏቸው ሠራተኞች ብዛት 686 እንደሚሆን ሪፖርተር በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ውስጥ 290 ቻይናውያንና 52 በመቶ ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንደሚሆኑ ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በሁለተኛው ዓመት የሚሳተፉ ቻይናውያን ወደ 24 በመቶ ዝቅ እንደሚል፣ በሦስተኛው ዓመት ደግሞ ወደ 13 በመቶ፣ በአራተኛው ዓመት ኢትዮጵያውያን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሩት ይሆናል፡፡
በኮንትራቱ መሠረት ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች የፈጠሩት ጥምረት በሦስተኛው ዓመት ላይ የቻይናዋ ሸንዘን ከተማ የደረሰችበት የባቡር ቴክኖሎጂ ወደ አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ ይዘዋወራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በመጨረሻዎቹ ሁለት የኮንትራት ዓመታት የቻይናዎቹ ኩባንያዎች ሚና ከኋላ ሆኖ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ነው፡፡

This content is published on, Reporter Wednesday December 2014 Page: 01

Hits: 731