በአሥር ቢሊዮን ብር የተገነባው የዳንጐቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ምርት ሊጀምር ነው

Published: Thursday, 26 March 2015 Written by Reporter Sunday 22 March 2015 Page: 04

Note : You need an Amharic Reader to read this content

-ከብድርና ከብክለት ነፃ ነው ተብሏል
-500 የጭነት ተሽከርካሪዎች ሊያስገባ ነው
-በፖታሽ፣ በጥጥና በስኳር ልማት ለመሳተፍ አቅዷል
በናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ በአሥር ቢሊዮን ብር ወጪ በሙገር አቅራቢያ የተገነባው ዘመዊው የሲሚንቶ ፋብሪካ በመጪው ሳምንት የሙከራ ምርት ይጀምራል፡፡
___________________

ከአፍሪካ ቀዳሚ ባለሀብት የሆኑት ሚስተር ዳንጐቴ ኩባንያ በሆነው ዳንጐቴ ሲሜንት ኢትዮጵያ በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አዳበርጋ ወረዳ የተገነባው ፋብሪካ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው፡፡ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሙገር ከተማ አቅራቢያ የተገነባው ዘመናዊ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ በ134 ሔክታር ላይ አርፏል፡፡ ከምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ የሲሚንቶ ፋብሪካ እንደሆነ የዳንጐቴ ሲሜንት ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ለማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ፋብሪካው ኦፒሲ፣ ፒፒሲና ለግድብ ግንባታ የሚውል ልዩ ሲሚንቶ ያመርታል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ የካቲት 2005 ዓ.ም. ተጀምሮ በአጭር ጊዜ በመጠናቀቁ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምሥጋና ደብዳቤ ለኩባንያው እንደተጻፈለት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፋብሪካውን ግንባታ ሥራ ኮንትራት ወስዶ ያከናወነው ሲኖማ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ የተሰኘ የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው፡፡ ሚስተር ዳንጐቴ የግንባታውን ሒደት በየሁለት ሳምንቱ በግል አውሮፕላናቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ተሾመ፣ ለፕሮጀክቱ ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡
የፋብሪካው ማሽኖች በሙሉ ከጀርመን፣ ከጣሊያንና ከስዊድን የተገዙ መሆናቸውን፣ በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ አለ የተባለ የሲሚንቶ ፋብሪካ ቴክኖሎጂ እንዳመጡ አቶ ተሾመ ገልጸው፣ ፋብሪካው የሚያመርተው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሲሚንቶ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የሲሚንቶ ከረጢቶች ወደ ጭነት ተሽከርካሪዎች የሚጫኑት በሮቦት ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ዘጠኝ ተሽከርካሪዎች ለመጫን የሚያስችል ሥፍራ አመቻችቷል፡፡ አንድ የጭነት ተሽከርካሪ ፋብሪካው ግቢ ገብቶ 800 ከረጢቶች ተጭኖ ለመውጣት ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ብቻ እንደሚፈጅበት ከሥራ አስኪያጁ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በምርት ጥራት ቁጥጥር ክፍል ሥራው የሚከናወነው በሮቦት በመታገዝ እንደሆነ የገለጹት አቶ ተሾመ፣ ፋብሪካው ጭስ አልባና ከብክለት ሙሉ በሙሉ ነፃ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ኩባንያው አሥር ቢሊዮን ብር ወጪ ሲያደርግ ምንም ዓይነት ብድር አለመውሰዱን ገልጸዋል፡፡
ለፋብሪካው የሚያስፈልገውን 40 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መድቧል፡፡ ከሱሉልታ ከተማ ፋብሪካው ድረስ 57 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና የሰብስቴሽን ግንባታ ሥራ ኩባንያው በራሱ ወጪ አከናውኗል፡፡
ዳንጐቴ ሲሜንት ሲሚንቶ የሚያመላልሱ 500 የጭነት ተሽከርካሪዎች በቅርቡ ከቻይና ማስገባት እንደሚጀምር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ፋብሪካው ከሦስት ሳምንት በኋላ ሚስተር ዳንጐቴና ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት እንደሚመረቅ፣ ምርቱን ከሚያዚያ ወር መጨረሻ ወይም ግንቦት መጀመሪያ ጀምሮ ለገበያ እንደሚያቀርብ አቶ ተሾመ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከፍተኛ ጥራት ያለው ሲሚንቶ በተመጣጣኝ ዋጋ የምናቀርብ በመሆኑ የገበያ ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም፤›› ብለዋል፡፡
ፋብሪካው ከ2,000 በላይ የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ከሲሚንቶ ፋብሪካ ተጨማሪ ዳንጐቴ ግሩፕ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖታሽ ማዕድን፣ በጥጥና በስኳር ልማት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው የኩባንያው ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዳንጐቴ በናይጄሪያ በዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የፔትሮ ኬሚካል ፋብሪካ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካና የነዳጅ ማጣሪያ በመገንባት ላይ ሲሆን ለማዳበሪያ ፋብሪካው ግብዓት የሚሆን ፖታሽ ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ኩባንያው የፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ፈቃድ እንዲሰጠው ለማዕድን ሚኒስቴር ማመልከቻ አስገብቷል፡፡
በተመሳሳይ ኩባንያው የጥጥና የሸንኮራ አገዳ ልማት ለማካሄድ ፍላጎት እንዳለው ለኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ገልጿል፡፡ ዳንጐቴ ሲሜንት በ17 የአፍሪካ አገሮች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የገነባ ትልቁ ሲሚንቶ አምራችና አቅራቢ ኩባንያ ነው፡፡ ዳንጐቴ የዳንጐቴ ስኳር፣ የዳንጐቴ ኢንዱስትሪና ዳንጐቴ የነዳጅ ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ፣ በፎርብስ ቱጃሮች ዝርዝር 67ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የ15.8 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ባለቤት ናቸው፡፡

This content is published on, Reporter Sunday 22 March 2015 Page: 04

 

Hits: 1002