የአዲስ አበባ አስተዳደር ለመሬት ዋጋ ንረት መንስዔ በስፋት አለመቅረቡ ነው አለ

Published: Thursday, 26 March 2015 Written by Reporter Wednesday 25 March 2015 Page: 03

Note : You need an Amharic Reader to read this content


በመሬት ሊዝ ጨረታ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ንረት መንስዔ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት በስፋት ባለማቅረቡ መሆኑን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናገሩ፡፡
___________________

ከንቲባ ድሪባ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አስተዳደሩ መሬት በስፋት ካለማቅረብ ጋር ተያይዞ የመሬት ዋጋ ሊጨምር ይችላል የሚሉ ግለሰቦች፣ ኢኮኖሚ ከሚፈቅደው በላይ የተጋነነ ዋጋ እያቀረቡ ነው ብለዋል፡፡
በአስተዳደሩ ክልል ውስጥ ለሚገኝ መሬት ኢኮኖሚው ከሚፈቅደው በላይ ዋጋ እየተሰጠ በመሆኑ፣ ይህንን አካሄድ መንግሥት የሚደግፈው እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ድሪባ፣ ‹‹ባለሀብቱ መሬት ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ከማፍሰስ ይልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ቢያውለው መልካም ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የመሬት ዋጋ ያላግባብ እንዲንር አንፈልግም፡፡ መሬት ሊያወጣ ከሚገባው በላይ ገንዘብ እንዲቀርብ መንግሥት አይፈልግም፤›› በማለትም ከንቲባ ድሪባ የመንግሥትን አቋም አስገንዝበዋል፡፡
ለመሬት የሚቀርበውን ዋጋ ለማረጋጋት መንግሥት በሰፊው ቦታ ማቅረብ እንደሚኖርበት የተናገሩት አቶ ድሪባ፣ ‹‹መሬት በውድ ገዝቶ የሕንፃውን ኪራይ በማናር ገቢ ለማግኘት የሚሞክሩ ግለሰቦችን መንግሥት አይደግፍም፤›› ብለዋል፡፡
ይህንን የመሬት ዋጋ ንረት ለማረጋጋት አስተዳደሩ በሰፊው መሬት ያቀርባል ያሉት ከንቲባ ድሪባ፣ ተጫራቾች መሬቱ ሊያወጣ የሚችለውን ዋጋ ብቻ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ ከንቲባ ድሪባ የሚመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በ2002 ዓ.ም. ሥልጣኑን ከተረከበ በኋላ በወጡት 13 ጨረታዎች፣ ለመሬት የሚቀርበው ዋጋ ከመረጋጋት ይልቅ እጅግ እየናረ በመሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ለቢዝነስ ቦታዎች ከ50 ሺሕ ብር በላይ በካሬ ሜትር ማቅረብ ከመለመድ አልፎ፣ ከወራት በፊት መርካቶ አካባቢ ለወጣ 500 ካሬ ሜትር የማይሞላ መሬት በካሬ ሜትር 305 ሺሕ ብር ቀርቧል፡፡
ለመኖሪያ ቤትም እንዲሁ ከ30 ሺሕ ብር በላይ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ለሁለቱም አገልግሎቶች እየቀረቡ የሚገኙት ዋጋዎች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ኢኮኖሚ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እጅግ የተራራቁና የተጋነኑ እንደሆኑ በርካታ ባለሙያዎች በየጊዜው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ በየወሩ ቦታ በብዛት የማቅረብ ዕቅድ ቢነድፍምና በተለይ በየወሩ ጨረታ ማውጣት ቢቻልም፣ ቦታ በብዛት ማቅረብ እንዳልተሳካለት ግን ተገልጿል፡፡
ከንቲባ ድሪባ ይህ የሥራ አፈጻጸም ደካማ መሆኑን አምነው፣ በቀጣይ የቦታ አቅርቦቱ እንደሚሻሻል አመልክተዋል፡፡

This content is published on, Reporter Wednesday 25 March 2015 Page: 03

 

Hits: 814