የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአንድ ቢሊዮን ብር ጨረታ ተሰረዘ

Published: Monday, 30 March 2015 Written by Reporter Sunday 29 March 2015 Page: 05

Note : You need an Amharic Reader to read this content

የመንግሥት ዕቃዎች ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ለአዲስ አበባ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዘመናዊ ማሠልጠኛ ተቋም ለመገንባት ያወጣውን የአንድ ቢሊዮን ብር ጨረታ ሰረዘ፡፡
___________________

የቦሌ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከቦታው እንዲነሳ የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ጠየቀ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከመገናኛ ወደ ቦሌ በሚወስደው ቀለበት መንገድ፣ ከአምቼ ፊት ለፊት በሚገኘው ቦታ በአንድ ቢሊዮን ብር ዘመናዊ የሥልጠና ማዕከል የመገንባት ዕቅድ አውጥቶ ነበር፡፡ ይህንን ግንባታ የሚያካሂድ ኩባንያ የመምረጥ ኃላፊነት በፌዴራል ደረጃ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የመንግሥት ዕቃ ግዢና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶትም ነበር፡፡
ኤጀንሲው ባወጣው ጨረታ በርካታ ኩባንያዎች ለመሳተፍ የተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ በግንባታው ውስጥ መካተት አለባቸው ያላቸው ሐሳቦች በመመንጨታቸው ጨረታው መሰረዙን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የከተማው ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት 30 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት አለው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የራሱና የቦሌ ፖሊስ ጣቢያ የሚጠቀምባቸው ሕንፃዎች ይገኛሉ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲሱ ግንባታ የሚካሄደው በ20 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በመሆኑ ግንባታውን ለማካሄድ የግድ ፖሊስ ጣቢያው መነሳት ይኖርበታል፡፡
ፖሊስ ጣቢያው ቦታ እስኪገኝለት ድረስ ለአንድ ዓመት እንዲጠቀም የተወሰነው በምክትል ከንቲባው አቶ አባተ ስጦታው ፊርማ በወጣ ደብዳቤ ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን ፖሊስ ጣቢያው የአንድ ዓመት ጊዜውን ቢያጠናቅቅም፣ በውሰት የተሰጠውን ሕንፃ ባለማስረከቡ ኢንስቲትዩቱ ቦታውን እንዲለቅ በደብዳቤ መጠየቁን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በዚህ ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ የልቀት ማዕከል የመገንባት ዕቅድ አለው፡፡ የልቀት ማዕከሉ የሰው ኃይል ሥልጠና፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማማከር፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እንደሚያካሂድ ተገልጿል፡፡
ግንባታው የተለያዩ አዳራሾች፣ መኝታ ክፍሎች፣ መዝናኛ ማዕከላትና ሌሎች ልዩ ልዩ ግንባታዎችን ያካሂዳል ተብሏል፡፡ ግንባታው የከተማው አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ በማድረግና መልካም አስተዳደርን በማስፈን በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሩክነሽ አረጋ በዚህ ጉዳይ ላይ ለጊዜው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

This content is published on, Reporter Sunday 29 March 2015 Page: 05

Hits: 901