የዓለም ባንክ ለፍጥነት መንገድ ማስፋፊያ 370 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቀደ

Published: Monday, 25 May 2015 Written by Reporter Sunday 24 May 2015 Page: 10

You need an Amharic Reader to read this content

 ዘንድሮ  ያፀደቃቸው  ፕሮጀክቶች  በጠቅላላው  950  ሚሊዮን  ዶላር  ብድር  አስመዝግበዋል

የዓለም  ባንክ  በዚህ  ሳምንት  አጋማሽ  ይፋ  ባደረገው  መረጃ  መሠረት  ለፍጥነት  መንገድ  ማስፋፊያ  ሥራዎች  የሚውል  370  ሚሊዮን  ዶላር  ወይም  7.4  ቢሊዮን  ብር  ብድር  አፅድቋል፡፡  ይህ  ገንዘብ  ከሚያስፈልገው  ጠቅላላ  ገንዘብ  ውስጥ  ከግማሽ  በላይ  የሚሸፍን  እንደሚሆን  ተገምቷል፡፡ 

ባንኩ ከዋሺንግተን ባወጣው መግለጫ መሠረት ብድሩን የለቀቀው ከባቱ (ዝዋይ) እስከ አርሲ ነገሌ ላለው የሞጆ - ሐዋሳ አዲስ የፈጣን መንገድ ግንባታ ሲሆን፣ መንገዱ የአገሪቱን ደቡባዊ ክፍሎች ከማዕከላዊና ሰሜናዊ አካባቢዎች ጋር እንደሚያገናኝ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጂቡቲ ወደብ በኩል ያለውን የንግድ በር መስመር በማጠናከር የምሥራቅ አፍሪካ አውራ መንገድ በመሆን ኢትዮጵያን ከኬንያ ባሻገር ከደቡባዊ አፍሪካ ጋር እንደሚያገናኝ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ 

ምንም እንኳ የዓለም ባንክ የ57 ኪሎ ሜትር ዝርመት ያለውን የመንገድ ግንባታ በ370 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመደገፍ ቢወስንም፣ ከሞጆ እስከ ሐዋሳ የሚዘረጋው የ203 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ግንባታ ላይ የፋይናንስ ድጋፍ በማቅረብ እየተሳተፉ የሚገኙት የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የኮሪያው የኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ፣ እንዲሁም የቻይናው ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ 57 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍነው መንገድ ግንባታ ድጋፍ እንደሰጠ ታውቋል፡፡ ባንኩ 126 ሚሊዮን ዶላር ብድር መልቀቁ የሚታወስ ነው፡፡ የኮሪያው ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ በበኩሉ ለ37 ኪሎ ሜትሩ መንገድ ግንባታ የ100 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ ሲያቀርብ፣ የቻይናው ባንክም የ52 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገዱን ግንባታ ለመደገፍ ፋይናንስ እንደሚያቀርብ የሚጠበቀው ሌላኛው አበዳሪ ተቋም ነው፡፡ አዲሱ የፍጥነት መንገድ በጠቅላላው 13 ቢሊዮን ብር የሚያስወጣ ሲሆን፣ ከአቃቂ እስከ አዳማ የተዘረጋው የፍጥነት መንገድ 11 ቢሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበት ይታወቃል፡፡

የፍጥነት መንገዱን ለማስፋፋት የዓለም ባንክ ከሰጠው የ370 ሚሊዮን ዶላር ብድር በተጨማሪ ዘንድሮ ከ950 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ለመስጠት መስማማቱን የባንኩ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህም ሆኖ ባለፈው ዓመት ለኢትዮጵያ መንግሥት የተፈቀደው ጠቅላላ የብድርና የዕርዳታ መጠን 1.646 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገበ በመሆኑ እስካሁን ባንኩ ለመንግሥት ካፀደቃቸው የፋይናንስ ድጋፎች ሁሉ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ካቻምና በባንኩ የተፈቀደው የገንዘብ መጠን 974 ሚሊዮን ዶላር መሆኑም ይታወሳል፡፡

 This content is published on: Reporter Sunday 24 May 2015 Page:  10

 

Hits: 871