ሁለት አዳዲስ አገር በቀል ኮንትራክተሮች የገነቡት መንገድ ለትራፊክ ክፍት ሊሆን ነው

Published: Tuesday, 16 June 2015 Written by Reporter Sunday 14 June 2015 Page: 10

You need an Amharic Reader to read this content

ፕሮጀክቱ  364  ሚሊዮን  ብር  በላይ  ወጪ  ተደርጐበታል

በሁለት  አዳዲስ  አገር  በቀል  ኮንትራክተሮች  364  ሚሊዮን  ብር  በላይ  በሆነ  ወጪ  የተገነባው  የሴሩ  ሸነን  ወንዝ  ሼክ  ሁሴንመንገድ  ግንባታ  ተጠናቅቆ  ከቀናት  በኋላ  ለትራፊክ  ክፍት  እንደሚሆን  ተገለጸ፡፡ 

የአርሲ ዞንን ከባሌና ከምዕራብ ሐረርጌ ያስተሳስራል የተባለው ይህ መንገድ ለኮንትራክተሮቹ የተሰጠው በሁለት ፕሮጀክት ተከፍሎ ነው፡፡ 54 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ይህ መንገድ፣ ለሁለት ተከፍሎ የተሰጠው ለአሠራር እንዲያመች መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ገልጿል፡፡ በአንደኛው ክፍል ከሴሩ እስከ ኪሎ ሜትር 23 የሚል ስያሜ የተሰጠውና 23 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን መንገድ ሳምሶን ቸርነት ጄኔራል ኮንትራክተር የገነባው መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከሴሩ ኪሎ ሜትር 23 እስከ ኪሎ ሜትር 59 ያለውን 36 ኪሎ ሜትር ደግሞ በዮሴፍ ተከተል ኮንትራክተር እንደተሠራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በሁለቱም ኮንትራክተሮች የተሠራው 59 ኪሎ ሜትር መንገድ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት መንገድ ያልነበረበት ሲሆን፣ ደረጃውን በጠበቀ የጠጠር መንገድ ደረጃ የተገነባ እንደሆነ የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ ከሆነ በአሁኑ ወቅት አንደኛው ክፍል የመንገድ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የሁለተኛው ክፍል ግን የአንድ ድልድይ ግንባታ የተወሰነ የማጠናቀቂያ ብቻ የሚቀረውና ከአጠቃላይ ሥራው ግን ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቋቋል፡፡ ይህም በጥቂት ቀናት ውስጥ መንገዱ ለትራፊክ ክፍት ሆኖ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በአጠቃላይ ስምንት ድልድዮች ያሉት ሲሆን፣ በርካታ የአፈር ቆረጣና ጠረጋ፣ የውኃ ቱቦች ቀበራ፣ የአቃፊ ግንብና ሌሎች የስትራክቸር ሥራዎችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡ 

የዚህ መንገድ ለትራፊክ ክፍት መሆን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ ድሬ ሼክ ሁሴን ዋሻ ለመሄድና ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሶፍ ዑመር ዋሻ ለመሄድ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሏል፡፡ በተለይ ወደ ሶፍ ዑመርና ድሬ ሼክ ሁሴን ዋሻዎችን ለሚጐበኙ ቱሪስቶች የመንገዱ መሠራት የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡  

ግንባታውን ያካሄዱት ሁለቱም አገር በቀል ኮንትራክተሮች ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ግንባታ ሥራ ሲረከቡ የመጀመሪያቸው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ ሳምሶን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ተሳትፎን ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት አቅማቸውን አጎልብተው ሥራውን እንዲያገኙ የተደረጉ ናቸው፡፡ 

በመንገድ ልማት ዘርፉ ለአገር በቀል የሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎችን ተሳትፎ በማሳደጉ ረገድ የተደረገውን ጥረት ተከትሎ የተረከቧቸው ሥራዎች በአግባቡ እየፈጸሙ መሆኑን የሁለቱ ተቋራጮች አፈጻጸም ምሳሌ ሊሆን ይችላል ያሉት አቶ ሳምሶን፣ ተወዳዳሪነታቸውን ከማሻሻል አኳያ ከፍተኛ የሆነ ፋይዳ ይኖረዋልም ብለዋል፡፡ 

ከግንባታ ሥራው ባሻገር የሁለቱንም የመንገድ ፕሮጀክቶች የማማከር ሥራ ተረክበው የሠሩት አገር በቀል አማካሪዎች መሆናቸውን ያስታወሰው የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ፣ ሥራውን በአገር በቀል ተቋራጭና አማካሪዎች ማሠራቱ የውጭ ምንዛሪን ከማዳን አንፃር የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ ነውም ይላል፡፡ 

አንደኛውን ክፍል ሥራ የማማከርና የቁጥጥር ሥራ የሠሩት ስታዲያ ኢንጂነሪንግ ሲሆን፣ ሁለተኛውን ደግሞ ኒች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ጎጎት ኢንጂነሪነግ የተባሉ አገር በቀል አማካሪዎች በጥምረት በመሆን ነው፡፡ 

ለመንገድ ፕሮጀክቱ የዋለውን ወጪ ሙሉ ለሙሉ የሸፈነው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡   

This content is published on ፡ Reporter Sunday 14 June 2015 Page: 10

 

Hits: 1117