ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተሾመ

Published: Tuesday, 16 June 2015 Written by Reporter Sunday 14 June 2015 Page : 01

You need an Amharic Reader to read this content

የጠቅላይ  ሚኒስትር  ጽሕፈት  ቤት  የሱር  ኮንስትራክሽን  ኩባንያ  የኮንስትራክሽን  ዲፓርትመንት  ኃላፊ  የነበሩትን  ኢንጂነር  አርዓያግርማይ  ፣የኢትዮጵያ  መንገዶች  ባለሥልጣን  ዋና  ዳይሬክተር  አድርጐ  ሾመ፡፡ 

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ አቶ አርዓያ ከሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን ይገልጻል፡፡ 

ኢንጂነር አርዓያ በዋና ዳይሬክተርነት መሾማቸውን ለሪፖርተር አረጋግጠው፣ መንግሥት በመንገድ ልማት ዘርፍ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ 

ኢንጂነር አርዓያ በ1987 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ትምህርት መስክ ተመርቀዋል፡፡ ከትምህርት ዓለም በኋላ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከጌዶ - ፊንጫ ድረስ ባካሄደው የመንገድ ግንባታ የፕሮጀክት ኃላፊ ሆነው መሥራታቸው ታውቋል፡፡

ኢንጂነር አርዓያ በ1999 ዓ.ም. በኤፈርት ሥር ተቋቁሞ በሥራ ላይ የሚገኘውን ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተቀላቅለዋል፡፡ 

የሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ታደሰ የማነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢንጂነር አርዓያ በ1999 ዓ.ም. ኩባንያውን እንደተቀላቀሉ በሰሜን ጎንደር ከሻውራ - ገለጎ ድረስ ለተገለነባው 147 ኪሎ ሜትር መንገድ የፕሮጀክት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ 

‹‹ይህ መንገድ እጅግ አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን፣ ኢንጂነር አርዓያ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበበት ነው፤›› በማለት ምስክርነታቸውን አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ከመነቤኛ - ለምለም በረሃ የተገነባውን መንገድ ጨምሮ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶችን መርተው በስኬት ማጠናቀቃቸውን ኢንጂነር ታደሰ አስረድተዋል፡፡ 

ኢንጂነር አርዓያ የአሁኑ ሹመት እስኪሰጣቸው ድረስ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሚያስገነባውን የዛሪማ ግድብ በኃላፊነት እየመሩ፣ ውጤታማ ሥራ መሥራታቸውን ኢንጂነር ታደሰ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢንጂነር አርዓያ ካሉን የፕሮጀክት ኃላፊዎች መካከል በውጤታማነታቸው ከሚታወቁት አንዱ በመሆኑ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት አምጥተን ለከፍተኛ ኃላፊነት አጭተነው ነበር፤›› በማለት የሚናገሩት ኢንጂነር ታደሰ፣ መንግሥት ለበለጠ ከፍተኛ ኃላፊነት ስለመረጣቸው ምንም ማድረግ አለመቻላቸውን የኢንጂነር አርዓያን ብቃት በማድነቅ ገልጸዋል፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ላለፉት አሥር ዓመታት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉትን አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልን፣ ከጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ማሰናበቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በቀለ አቶ ዛይድን በመተካት የራሳቸውን ሥራ ጨምረው ላለፉት ስምንት ወራት በተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ሳምንት ኢንጂነር አርዓያ ሥራቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

This content is published on ፡ Reporter Sunday 14 June 2015 Page : 01

Hits: 1063